በአንድ የዘመዴ ቤት
አንድ ዘመዴ ቤት ሄጄ ነው፡፡ እናቱ «እስኪ ያንን ነገር ለዳንኤል አሳየው» አለቺው ልጇን፡፡ ልጇ የአራተኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ ደብተሩን ይዞት መጣ፡፡ ትናንት ሠርቶ ዛሬ ባሳረመው የአማርኛ የቤት ሥራ ሁለት ኤክስ አግኝቷል፡፡ ልጁ ግን ለምን ኤክስ ሊሆን እንደቻለ ሊገባው አልቻለም፡፡ እናቱን ደጋግሞ ጠየቃት፡፡ እርሷም ግልጽ አልሆነላትም፡፡
የተሰጠው ጥያቄ አዛምድ ነው፡፡ እዚያ መካከል «እንደ ወትሮው» የሚል ሐረግ በ «ሀ» ሥር ይገኛል፡፡ በ «ለ» ሥር ደግሞ «እንደ ሁልጊዜው» የሚል ምርጫ አለ፡፡ ልጁ የመጀመርያውን ኤክስ ያገኘው እነዚህን በማዛመዱ ነበር፡፡ ከዚያው በታች በ«ሀ» ሥር ላለው «መሞከር» ለሚለው ቃል «መጣር» የሚል ተዛማጅ በ«ለ» ሥር ተቀምጧል፡፡ የሚል ሌላ አዛምድ አለ፡፡
ልጁ ከተሰጡት መልሶች ተቀራራቢ የሆነውን መልሷል፡፡ መምህሩ ግን አላረመለትም፡፡ እኔንም ጥያቄ ፈጠረብኝ፡፡ ይበልጥ ያስገረመኝ ደግሞ ትክክለኛው መልስ ምን እንደሆነ አለመጻፉ ነው፡፡ ልጁን «መልሱ ምንድን ነው አላችሁ?» ብዬ ጠየቅኩት፡፡ «ኤክስ አደረገኝ እንጂ መልሱን አልጻፈልኝም» አለኝ፡፡ መምህሩ ደብተራቸውን ወስዶ ኖሯል ያረመው፡፡
«እስኪ መጽሐፉን አምጣ» አልኩና ጥያቄዎቹን መመልከት ጀመርኩ፡፡ አሁን ነገሩ ግልጽ ሆነልኝ፡፡ ልጁ «መ»ን እና «ሠ»ን ሲገለብጥ አቀያይሯቸዋል፡፡ መምህሩም የአዛምዱን መልሶች ያረመው ፊደላቱን እያየ እንጂ መልሱን እያየ አይደለም፡፡ ይህ ግን በልጁ ላይ ሁለት ነገር ፈጠረበት፡፡ አንደኛ ለምን ኤክስ እንዳገኘ ሊገባው አልቻለም? ሁለተኛ ደግሞ የእነዚህን ሐረጋት ትርጉም ሊያውቅ አልቻለም፡፡ ምክንያቱም እርሱ ትርጉም ነው ብሎ የሰጠው መልስ ስሕተት ነው ተብሏል፡፡ ትክክለኛው ደግሞ አልተነገረውም፡፡