Monday, November 12, 2012

ከተራራው ጀርባ ያለው ሰው

ምንጭ:-http://www.danielkibret.com

እስኪ ታላቅ ነው በምንለው ቦታ ደርሰናል ብለን የምናስብ ሰዎች ለአፍታ ዘወር ብለን ተንጠላጥለንባቸው የተሻገርንባቸውን አያሌ ሰዎች ለማስታወስ እንሞክር፡፡ እዚህ ለመድረሳችን የምናውቀውንም የማናውቀውንም ድርሻ የተወጡ፣ እነርሱነታቸው እኛነታችን ውስጥ ያለ፡፡ አሁን የተቀመጥንበት ወንበር፣ የምንተኛበትም አልጋ፣ የምንኖርበትም ቤት፣ የምንቆጥረውም ብር፣ የወጣንበትም ከፍታ የእነርሱ ጭምር የሆነ፡፡ እነርሱ ባይኖሩ ኖሮ እዚህ ቦታ ለመድረስ ቀርቶ ወደዚህ አቅጣጫ እንኳን ለማየት የማይቻለን፡፡ እስኪ የሚቀጥለውን ታሪክ እየተከታተላችሁ እነዚህን አስቧቸው፡፡
መምህራን፣ የቤት ሠራተኞች፣ ሞግዚቶች፣ የሠፈር ሽማግሌዎች፣ አያት፣ አጎት፣ አክስት፣ የጥበቃ ሠራተኞች፣ ሾፌሮች፣ ጓደኞች፣ ሐኪሞች፣ ፖሊሶች፣ አንድ መሥሪያ ቤት ሄደን በጎ ያደረጉልን ሰዎች፣ ሳያስቡትም ሳናስበውም ዕድል የከፈቱልን ሰዎች፣ ሕይወታችንን የቀየረችውን አንዷን ብር የሰጡን ሰዎች፣ ከሞት ያተረፉን፣ ከመከራ የታደጉን ሰዎች፤ ያበረታቱን፣ ያጨበጨቡልን፣ የመረቁን፣ መንገድ ያሳዩን፣ በልብሳቸው አጊጠን፣ በምግባቸው ጠግበን እንድንጓዝ የረዱን፤ ከኛ በፊት ሕይወታቸውን ሰጥተው፣ ለኛ ሲሉ ተሠውተው ያለፉልን ጀግኖች፤ እነማን ነበሩ? እስኪ ይህንን ታሪክ እያነበባችሁ አስቧቸው፡፡
 ሁለት ባልንጀሮች በመርከብ ሲጓዙ በባሕር መካከል መርከባቸው ትሠበርባቸዋለች፡፡ ሁለቱም በመርከቧ ስባሪ ላይ ሆነው ውጭ ነፍስ ግቢ ነፍስ ከማዕበሉ ጋር ሲታገሉ ነፋስ እየገፋ ወደ አንዲት ደሴት ያደርሳቸዋል፡፡ ሁለቱም ከሞት በመለስ ሲነቁ በደን በተሞላች ደሴት ውስጥ ራሳቸውን ያገኙታል፡፡ ጥቂት ጊዜ አብረው ከቆዩ በኋላ ምንም አማራጭ ስላልነበራቸው ደሴቲቱን ለሁለት ተካፍለው ለመኖር ተስማሙ፡፡ በዚህም መሠረት በደሴቲቱ መካከል ካለው ተራራ ፊት ለፊት ያለውን አንዱ ጀርባውንም ሌላው ወሰደ፡፡
ሁለቱም ባገኙት መሣርያ ሊሠሩ፣ በየጊዜው እየተገናኙ ሊወያዩና ሊጠያየቁ፣ ብሎም በርትተው ሊጸልዩ ተስማሙ፡፡ በስምምነታቸውም መሠረት ወደ ደረሳቸው ቦታ ተጓዙና ሕይወትን ጀመሯት፡፡ መጀመርያ ከዛፉ እየዘነጠፉ ቤት መሳይ ነገር ሠሩ፡፡ ከዚያም ደግሞ የዱር ፍራፍሬ መለቃቀሙን ጀመሩ፡፡
ከተራራው ፊት ለፊት ያነበረው ሰው በጠዋት ተነሥቶ እግዚአብሔር ቤቱን እንደ ጥንት ቤቱ እንዲያደርግለት ጸለየ፡፡ ካጎነበሰበት ሲነቃም ትናንት በቅጠል የሠራው ቤት ምርጥ ቪላ ሆኖ አገኘው፡፡ የሰበሰበውንም ፍራፍሬ እዚያ በየመልኩ አስቀመጠ፡፡ በማግስቱም አምላኩ ቤቱን በቤት ዕቃዎች እንዲሞላለት ለመነ፡፡ ከጸሎቱ በኋላም እንዳለው ሆነለት፡፡ እርሱም እንጨት ሰብስቦ ፍራፍሬዎችን እያበሰለ ተመገበ፡፡
ከጥቂት ቀናት በኋላም እግዚአብሔር ሚስት ይሰጠው ዘንድ ለመነ፡፡ በማግሥቱም አንዲት ቆንጆ ሴት እየዋኘች ወደ ደሴቱ ስትመጣ አያት፡፡ ዐወቃትም፡፡ እርሷን ሲያገኝ ደግሞ ልጆችን ፈለገ፡፡ እነሆም ልጆችን አገኘ፡፡ መኪናም ተመኘ፤ እነሆም አገኘ፤ ታላላቅ ፎቆችን ማየትም ተመኘ፤ እነሆም አገኘ፡፡
በየወሩ መጨረሻ ከዚያኛው ጓደኛው ጋር ተገናኝተው ይነጋገሩ ነበር፡፡ ያኛው ጓደኛው እርሱ ከሚኖርባት በቅጠል የተሠራች ጎጆ በቀር ምንም አልነበረውም፡፡ በየጊዜው ይህኛው እያለፈለት ሲሄድ ያኛው ባለበት እየረገጠ ነው፡፡ ይህኛው ጸሎቱ መልስ ሲያገኝ ያኛው ግን ጸሎት እንጂ መልስ አልነበረውም፡፡ ይህኛው ሲጨመርለት ያኛው ግን ሕይወት እንደረጋችበት ናት፡፡
ጓደኛው ግራ ተጋባ፡፡ ‹‹ይህ ጓደኛዬ ኃጢአተኛ ሰው ነው ማለት ነው፡፡ ምናልባትም መርከባችንን የሰበራት እርሱ እንደ ዮናስ ኃጢአት ሠርቶ በመኮብለሉ ይሆናል›› ብሎ ገመተ፡፡ የራሱንም ጽድቅ አሰበና እጅግ ደስ አለው፡፡ ከዚህ አካባቢ ይህንን ኃጢአተኛ ሰው ትቶ መውጣት እንዳለበትም ወሰነ፡፡ አብረው አድገው አብረው በመርከብ ተጉዘው፣ አብረው በመርከብ አደጋ ተካፍለውና አብረው ወደ ደሴቷ በመጡ ሁለት ጓደኛሞች መካከል እንዴት ይህንን ያህል ልዩነት ሊከሰት እንደቻለ አልገባውም፡፡ እርሱ ባለ ቤት፣ ባለ ሚስት፣ ባለ ገንዘብ፣ ባለ መኪና፣ ባለ ፎቅ ሆኗል ያ ግን ‹ያ› እንደሆነ ው፡፡
ባለ ሀብት፣ ባለ ንግድ፣ ሚሊየነር፣ ቢሊየነር መሆን ተመኘ፡፡ ለዚህ ደግሞ መጀመርያ ደሴቲቱን ለቅቆ መውጣት አለበት፡፡ እናም ከዚህ ደሴት ይዞት የሚያወጣው መርከብ ይልክለት ዘንድ እግዚአብሔርን ለመነው፡፡ እግዚአብሔርም አንድ ትልቅ መርከብ ላከለት፡፡
ዕቃውን ጫነ፤ ሀብቱንም ሰበሰበ፡፡ ሚስቱንና ልጆቹንም አሳፈረ፡፡ ያኛውን ጓደኛውን ግን ሊሰናበተው እንኳን አልፈለገም፡፡ ርግጥ ነው አብረው ክፉና ደግ አሳልፈዋል፤ አብረው ታግለዋል፣ አብረው ተጉዘዋል፣ አብረው መርከ ባቸውን አጥተዋል፣ አብረው እዚህ ደርሰዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ‹ተለያየን› ወንዝ ላይ ደርሰዋል፡፡ አሁን ሁሉም ነገር ተረት መሆን አለበት፡፡
ወደ መርከቧ ገብቶ የመርከቧን መሪ ጨበጠ፡፡ ነገር ግን መርከቧ ልትነሣ አልቻለችም፡፡ ቀድሞ የሚያውቃቸውን ዕውቀቶች ሁሉ ሞከረ፡፡ ይህችን መርከብ ግን ማስነሣት አልተቻለውም፡፡ የመርከቧ ዕቃዎች አዳዲሶች ናቸው፡፡ የተበላሸ ነገር አይታይባትም፡፡
እጅግ ሲጨንቀው ወደ ፈጣሪው ለመነ፡፡ ፈጣሪም መልስ ሰጠው፡፡
‹‹ጓደኛህን ጥለህ ለመውጣት ለምን ፈለግክ?››
‹‹ይህ ጓደኛዬ ፈጣሪ የተጣላው ነው፡፡ ይጸልያል ነገር ግን አይመለስለትም፡፡ ምናልባትም አንዳች ችግር ቢኖርበት ይሆናል፡፡ ይህ ሁሉ በረከት እኔ ብቻዬን በጸሎት ያገኘሁት ነውና እርሱን መጨመር አይገባኝም›› አለው፡፡
ፈጣሪም መልሶ ‹‹ ለመሆኑ ይህ ሁሉ የተደረገልህ ለምን ይመስልሃል?›› አለው፡፡
‹‹ከልቤ ስለጸለይኩና ጸሎቴም መልስ ስላገኘ ነው›› አለው፡፡
‹‹አይደለም›› ሲል ፈጣሪ መለሰለት፡፡
‹‹ታድያ ለምንድን ነው?›› አለና ጠየቀው፡፡
‹‹በጓደኛህ ምክንያት ነው›› አለው ፈጣሪም፡፡ አሁን ይበልጥ ግራ ተጋባ፡፡
‹‹ይህማ ሊሆን አይችልም፤ እርሱ እንኳን ለእኔ ለራሱም መሆን አልቻለም››
‹‹ሁለታችሁን የለያችሁ የጸለያችሁት ጸሎት ነው››
‹‹እንዴት?››
‹‹አንተ ይህንንና ያንን  ስጠኝ እያልክ ትጸልይ ነበር፡፡ እርሱ ግን እባክህን ‹ጓደኛዬ የሚለምንህን ስጠው› እያለ ነበር የሚጸልየው፡፡ ይህንን ሁሉ ያገኘኸውም ባንተ ሳይሆን በርሱ ጸሎት ነው፡፡ ያንተ ጸሎት የተሰማው በእርሱ ጸሎት ምክንያት ነው፡፤ አንተ የከበርከው፣ ባዕለ ጸጋ የሆንከው፣ ሀብት የሰበሰብከው፣ ያሸነፍከውና ዛሬም ለመውጫ የሚሆን መርከብ ያገኘኸው በእርሱ ምክንያት ነው፡፡ እርሱ ከራሱ ይልቅ ለአንተ በማሰቡ ነው፡፡ አንተ ግን ስለ ራስህ ብቻ የምታስብ ስስታምና ስግብግብ ነህ፡፡ ማካፈልን የማትወድ፣ መነሻህንም የምትረሳ ነህ፡፡
‹‹በሌሎች ትግል ለሥልጣን የበቁ፣ በሌሎች ንግድ ያተረፉ፣ በሌሎች ፈተና እነርሱ ያለፉ፣ በሌሎች ሥራ እነርሱ ደመወዝ የተከፈላቸው፣ ሌሎቹ ታመውላቸው እነርሱ በጤና የሚኖሩ፣ ሌሎቹ መርፌውን ተወግተውላቸው እነርሱ የዳኑ፣ ሌሎቹ አዝነውላቸው እነርሱ የሚደሰቱ አያሌ ናቸው፡፡ የሁሉም ችግር ግን እንዳንተ ዓይነት ነው፡፡ ‹ይህ ሁሉ የተገኘው በእኔ ብቻ ነው› ብለው ያስባሉ፡፡
ለእነርሱ እዚህ ቦታ መድረስ አብረዋቸው የለፉትን እንዲያውም ከእነርሱ በላይ የደከሙትን ይረሳሉ፡፡ እነርሱ ካገኙት ጥቂት እንኳን ሊያካፍሏቸው ፈቃደኞች አይደሉም፡፡ እስኪ ጳጳሳትን አስተምረው ለዚህ ያበቁትን የአብነት መምህራን ተመልከት፡፡ አሁን እነርሱን የሚያስታውሳቸው አለ? በጳጳሳቱ ሕይወት ውስጥ የአብነት መምህራኑ አስተዋጽዖ አለ፡፡ በአብነት መምህራኑ ሕይወት ውስጥ ግን የጳጳሳቱ አስተዋጽዖ የለም፡፡
እስኪ እናንተን አስተምረው ለዚህ ያበቋችሁን ከአንደኛ እስከ ኮሌጅ ያሉትን መምህራን አስታውስ፡፡ ይህ ሁሉ ባለ ሀብት፣ ባለ ሥልጣንና ባለ ጊዜ የእነዚህ ሰዎች አሻራ አርፎበታል፡፡ ግን እነርሱ የት ናቸው? እናንተስ የት ናችሁ? ለመሆኑ ሀገራችሁ እዚህ ስትደርስ በስንት ሰዎች ትከሻ ላይ ተራምዳ ነው፡፡ እነዚያ ሀገር የተራመደችባቸው ሰዎች ግን ዛሬ የት ናቸው? እንኳን ካገኛችሁት ልታካፍሏቸው ቀርቶ ስማቸውንስ በበጎ ታነሡታላችሁ? አሁን እናንተ የምትበሉትኮ አባቶቻችሁ ወታደሮች ሆነው አድዋና ማይጨው የዘመቱበት፣ አምስት ዓመት ከጣልያን ጋር የተዋጉበትን ደመወዛቸውን ነው፡፡ እነርሱ አልተከፈላቸውም፤ እነርሱ መረማመጃ ሆኑ እንጂ አልተረማመዱም፡፡ እናንተ ግን በእነርሱ ትከሻ ላይ ናችሁ፡፡
አሁን ከባለ ሥልጣን እስከ ተራው ድረስ የምትበሉት እነርሱ ሊከፈላቸው ሲገባ ሳይከፈላቸው ትተውት የሄዱትን ደመወዛቸውን ነው፡፡ ይህንን አስተውል፡፡ ይኼ ከተማዋን የሞላት ፎቅና ሕንፃ የባለቤቶቹ ብቻ እንዳይመስልህ፤ የብዙ ሰዎች ጭምር ነው፡፡ ልዩነቱ ሥራውን አብረው ሠሩት ፣ ምግቡን ግን ለብቻ በሉት፡፡ እነዚህ በሥልጣን የምታያቸው ሰዎች ብቻቸውን ታግለው፣ ብቻቸውን ሞተው፣ ብቻቸውን እዚህ የደረሱ እንዳይመስልህ፡፡ ብዙ ሺ ዎች፣ የሚታወቁና የማይታወቁ፣ የተመዘገቡና ያልተመዘገቡ፣ ይህቺን ቀን ያዩና ያላዩ አብረው ነው የታገሉት፣ አብረው ነው የሞቱት፤ ነገር ግን ጥቂቶች ናቸው አዲስ አበባን ማጣጣም የቻሉት፡፡ ‹‹በሺ ቢታለብ ያው በገል ነው›› ያለችውን የድመት ተረት እየተረቱ የተቀመጡ ሚሊዮኖች ናቸው፡፡ እንደዚህ እንዳንተ መርከቡ ሲመጣ ማንም እነርሱን አያስታውሳቸውም፡፡ 
እና ልጄ፣ ይኼ እስከዛሬ እየጸለየ እዚህ ከፍታ ላይ ያደረሰህን ወዳጅህን ረስተህ ብቻህን እሄዳለሁ ካልክ፣ እየጸለየ ሊያወርድህ እንደሚችልም አስብ፣ በርሱ እንደበለጸግክ ሁሉ በርሱ ልትደኸይ ትችላለህ፡፡ ቁልፉ አንተ ጋር ሳይሆን እርሱ ጋ ነው፡፡ ‹በረዥም ገመድ የታሠረች ጥጃ ገመዱ ሲላላ ገመዱ የሌለ ይመስላታል› እንደሚባለው ገመዱ ላልቶ ነው እንጂ አለ፡፡ ለዚህም ነው እሄዳለሁ ስትል ስቦ ያቆመህ፡፡››
ከመርከቡ ወርዶ በፍጥነት ወደ ተራራው ጀርባ መሄድ ላይ ነበር፡፡ ልጆቹና ሚስቱም ተከተሉት፡፡
ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው፤ በተመሳሳይ ኅትመት ላይ ማውጣት ነውር ነው፡፡
 

No comments:

Post a Comment