Monday, September 26, 2011

For the preaching of the cross is to them that perish foolishness; but unto us which are saved it is the power of God.

የመስቀል  በዓል የሚከበረው መስከረም ፲፯ ነው። ይህም በዓል በክርስቲያኑ ዓለም ሁሉ ይከበራል። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚነግረን ጌታ በመስቀል ሞቶ ከተነሳ በኃላ ሕሙማን መስቀሉን እየዳሰሱ በመስቀሉ እየታሹ ይፈወሱ ነበር።በዚህ በዙዎች የክርስትና እምነት ተከታዮች ሆኑ በክርስቶስ አመኑ። ይህንን የተመለከቱ አይሁድ መስቀሉን በአንድ ቆሻሻ መጣያ ቦታ ጣሉት የአካባቢው ኗሪ በዚያ ቆሻሻን እንዲጥል አደረጉት ስፍራውም እንደ ተራራ ጉብታ ሆነ፤ መስቀሉ በዚህ ስፍራ ለሶስት መቶ ዓመታት ቆይቷል። በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የንጉስ ቆስጠጢኖስ እናት ንግስት እሌኒ ይህን ታሪክ ትሰማ ነበርና ጉዞዋን ወደእየሩሳሌም ቀጠለች። በስፍራው ያለውን ጉብታ ቦታ ብታስቆፍርና በአካባቢው የሚገኙትን ብትጠይቅ ልታገኘው አልቻለችም ይሁንና መስቀሉ እንዲወጣ የእግዚአብሔር ፍቃድ ስለነበረ አንድ አረጋዊ ስሙ ኪርያኮስ የሚባል የእሌኒን መቸገር አይቶ እንደሚከተለው ይመክራታል። " አንቺም በከንቱ አትድከሚ ስውንም አታድክሚ እንጨት አሰብስበሽ እጣን አፍሽበት በእሳትም አያይዢው የእጣኑ ጢስ ወደላይ ወጥቶ ወደታች ሲመለስ አቅጣጫውን አይተሽ አስቆፍሪው በዚህ ምልክት ታገኚዋለሽ አላት እርሷም ያላትን ሁሉ አደረገች። በዚህም ታላቅ ምልክት የተደበቀውን መስቀል አውጥታዋለች።
በመስከረም ፲፮ ባላገሩ በቀበሌው የከተማው ህዝብ በተዘጋጀለት ቦታ ከየቤቱ ችቦውን እንጨቱን እያመጣ ይደምራል። ካህናቱም በደመራው ፊት ለፊት ጸሎት አድርሰው " መስቀል አብርሃ በክዋክብት አሰርገወ ሰማየ እምኩሉሰ ፀሐየ አርአየ" እያሉ ደመራውን ይዞራሉ ቀጥሎም ህዝቡ "እዮሀ አበባዬ መስከረም ጠባዬ" እያሉ በደመራው ዙሪያ ይጨፍራሉ። ማታ ሕዝቡ ችቦውን እያበራ ደስታውን ሲገልጥ ያመሻል በ፲፯ ጧት ደመራው ይለኮሳል አመድ እስኪሆን ድረስ ይቃጠላል ደመራው የተጸለየበትና የተባረከ ስለሆነ ሕዝቡ አመዱንና ትርኳሻውን እየተሻማ ወደ ቤቱ ይዞ ይሔዳል። ለሰውም ሆነ ለከብት መድኃኒት ሆኖ ያገልግላል።
ምንጭ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ   በብፅ አብነ  ጎርጎርዮስ የሸዋ ሊቀ ጳጳስየመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና።የጥበበኞችን ጥበብ አጠፋለሁ የአስተዋዮችንም ማስተዋል እጥላለሁ ተብሎ ተጽፎአልና።ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የት አለ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን?በእግዚአብሔር ጥበብ ምክንያት ዓለም እግዚአብሔርን በጥበብዋ ስላላወቀች፥ በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና።መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፥እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፥    (፩ኛ ቆሮ 1፡18)

አበው ይናገሩ

ምንጭ :http://www.eotcmk.org አትም ኢሜይል
ዘርዓቡሩክ ገ/ሕይወት

እስኪ ቀስቅሷቸው አበው ይናገሩ
የምንኩስና ግብር ምን ነበር ምሥጢሩ
የክርስትና ሕይወት ምን ነበር ተግባሩ
መቃብሩን ክፈቱና አበው ይመስክሩ፡፡

እኔስ ሰው አማረኝ የሃይማኖት ጀግና
ወልድ ዋሕድ ብሎ በእምነቱ የፀና
ጀግና ሰው አማረኝ ጠላት አሳፋሪ
ንጽህት ድንግል ብሎ እምነቱን መስካሪ፡፡

ነብያት በመጋዝ የተሰነጠቁት
ሐዋርያት ቁልቁል የተዘቀዘቁት
ሰማዕታት በእሳት የተለበለቡት
ቅዱሳን በገዳም ደርቀው የተገኙት
ምሥጢሩ ምን ነበር? አበው ይናገሩት፡፡

ይናገር ዝቋላ ግሸን ላሊበላ
የቅዱሳንን ዐፅም ለምን እንዳልበላ፡፡
ዋልድባ ይናገር ዜጋመልም ሳይቀር
እንባቸው መፍሰሱ ለምን እንደነበር፡፡
ነበር ወይ ፈልገው ሹመት ሽልማት?
ወይስ ሀብት ንብረት የተሟላ ቤት?
ወይስ አምሯቸው ነው ፈልገው መሞት?
እናንተ ገዳማት ምሥጢሩን አውሩት፡፡

ጐበዝ ሰው አማረኝ በእምነቱ የፀና
ምግባር ሃይማኖቱ በእጅጉ የቀና፡፡
እንጦንስ የወለደው በምግባር በእምነት
ተምሮ ያደገ ከተክለሃይማኖት፡፡
የጊዮርጊስ ወገን የት ነው የማገኘው?
በመሀል ከተማ በአራዳ ውስጥ ነው?
ወይስ በዝቋላ በደብረ ሊባኖስ በደብረ ዳሞ ነው?

ወገን ሰው ናፈቀኝ ዐይኔን ሰው አማረው
የሃይማኖት ጀግና የትነው የማገኘው?
ልግባ ወይ ዋልድባ ጫካ ካለበት
ማኅበረ ሥላሴ ከቅዱሳን ቤት?
አክሱም ግሸን ማርያም ከቃል ኪዳን ቦታ
ይገኛል ወይ ጀግና ጠላት የሚረታ?
ፈሪሐ እግዚአብሔር በልቡ ያደረ
ቤተ ክርስቲያንን ያልተደፋፈረ፡፡

የት ነው የማገኘው ለሃይማኖቱ ሟች
ለተዋሕዶ እምነት ጠበቃ ተሟጋች፡፡
የወገን መመኪያ የከሀዲ መቅሰፍት
ማነው እሱ ጀግና ተኝቶ እንደሆነ ይነሣ ቀስቅሱት፡፡
እስኪ ቀስቅሷቸው አበው ይናገሩ
የምንኩስና ግብ ምን ነበር ምሥጢሩ?
የክርስቲያን ሕይወት ምን ነበር ተግባሩ?
መቃብሩን ክፈቱት አበው ይመስክሩ፡፡

ወገን ሰው ናፈቀኝ ዐይኔን ጀግና አማረው
በእምነቱ የፀና የትነው የማገኘው?
ብቅ ይበል እንየው እሱ ማነው ጀግና?

በጐችን ከተኩላ ነቅቶ የሚጠብቅ
መከራ ቢከበው ከቶ የማይሰቀቅ
የሃይማኖት ጀግና ቆራጥ ሰው ገበሬ
እንደዚያ እንደ ጥንቱ ይገኛል ወይ ዛሬ?
የወገን የዘመድ ጥቅም ያላወረው
የመናፍቆች እጅ ኪሱን ያልዳበሰው
የዓለም አሸክላ ልቡን ያልማረከው
የክርስቶስ ወዳጅ እሱ ጀግና ማነው?
ምሥጢርን ከምሥጢሩ አንድ አድርጐ ቀምሮ
ወልድ ዋሕድ ብሎ ሃይማኖት መስክሮ
እንጦንስን መቃርስን በልቡ ያኖረ
ከአትናቴዎስ ከቄርሎስ ጥበብ የተማረ፡፡

ድንግል እመቤቴ ብሎ የሚመሰክር
መሆኗን የሚያምን ማኅደረ እግዚአብሔር
ቋቅ እንትፍ ብሎ የጠላ ክህደትን
ትንታግ ምላስም ጭንግፍግፉን
ልሳነ ጤዛ መናፍቅን
ወልደ አርዮስ ዲቃላውን፡፡
በሰይፈ ሥላሴ የሚቀላ
ጀግና ማነው ዝቅ ይበላ፡፡

ነበር ወይ ያን ጊዜ ለሹመት መጓጓት
እስኪ ጎርጎርዮሰ ይምጣና ጠይቁት
ፍቅርንም ይጠየቅ አባ ሕርያቆስ
ምሥጢርን ጠባቂ ወይም አባ መቃርስ፡፡

የክርስቶስ ባርያ የአጋንንት መቅሰፍት
ወንጌል አስተማሪ የሃይማኖት አባት
ይህንን ጉድ እንዲያይ ይምጣ ተክለሃይማኖት
የጸሎት ገበሬ ገብረ መንፈስ ቅዱስንም ይነሣ ቀስቅሱት
ይነሣ ጊዮርጊስ ይመስክር ምሥጢር
የሃይማኖት ፍቅር ምን እንደነበር፡፡

ከእናቶቻችንም አሉ ለፍጥረት ያዘኑ
ዲያብሎስ እንዲማር ጌታን የለመኑ፡፡
ስንቱን ልዘርዝረው የአባቶችን ሙያ
መር ብለው የወጡት ከሥጋ ገበያ
ጾም ጸሎት ነበረ የሃይማኖት ጋሻ
መልከስከስ ምንድነው እንደ አበደ ውሻ፡፡

እንደ መስኖ ውሃ ከነዱት መነዳት
ዓላማው ምንድነው የዘመኑ ወጣት፡፡

እኔስ ሰው አማረኝ የሃይማኖት ጀግና
ወልድ ዋሕድ ብሎ በእምነቱ የፀና
ዐይኔን ሰው አማረው ጀግና ሰው ገበሬ
ሃይማኖት መስካሪ እንደ ጥንቱ ዛሬ፡፡
ምንጭ፡- መለከት 1ኛ ዓመት ቁጥር 6