Wednesday, November 30, 2011

“ታቦተ ጽዮን” ፤ “ኅዳር ጽዮን“ ፤ “አክሱም ጽዮን “

ክፍል -2 የቀዳማዊ ምኒልክ ጉዞና የታቦተ ጽዮን መምጣት ቀዳማዊ ምኒልክ ከአደገ በኋላ በ12 ዓመቱ ከእናቱ የተሰጠውን ለታቦተ ጽዮንና ለንጉሥ ሰሎሞን እጅ መንሻ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ተጓዘ፡፡ ንግሥት ሳባም ለንጉሥ ሰሎሞን “ንጉሥ ሆይ ልጄን ሙሴ የጻፋቸውን ሕግጋት ሥርዓተ ክህነት አስተምረህ ላክልኝ፡፡” የሚል መልእክት ልካ ነበር፡፡ ቀዳማዊ ምኒልክ በኢየሩሳሌም ከአባቱ ዘንድ ለሦስት ዓመት ያህል ቆይቷል፡፡ በዚሁ ዘመን መጻሕፍተ ሙሴን፣ ሕገ መንግሥትን፣ ሥርዓተ ክህነትን የዕብራይስጥን ቋንቋ ከሊቀ ካህናቱ ከሳዶቅ ተምሯል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስም በፈቃደ እግዚአብሔር ታቦተ ጽዮንን ይዞልን መጥቷል፡፡ ይህች ታቦት ለ3000 ዓመታት ያህል እስከዛሬ ድረስ በኢትዮጵያ በአክሱም ትገኛለች፡፡ ንግሥት ሳባም ታቦተ ጽዮን መምጣቷን ስትሰማ ለእግዚአብሔር መስዋዕት አቀረበች፡፡ ሰዎችን መርጣ ታቦተ ጽዮንን እንዲጠብቁ አድርጋለች፡፡ የመንግሥቱን ሥልጣን በሙሉ ለቀዳማዊ ምኒልክ አስረክባ ከዚህ ዓለም በሞተ በተለየች ጊዜ በዚያው በአክሱም ተቀብራለች፡፡ ቦታውም እስከ አሁን ድረስ የንግሥት ሳባ መቃብር እየተባለ ይጠራል፡፡ በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው ታሪክ ጸሐፊው አቡሳላህ “አቢሲኒያውያን በእግዚአብሔር ጣቶች አሥርቱ ቃለት የተጻፈባት፣ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ያሉባት የቃል ኪዳኑ ታቦት አለቻቸው፡፡” በማለት ጽፎ ነበር፡፡ በዘመናችን ይህችን ታቦት ፍለጋ ያደረገው ግርሃም ሐንኮክም “The sign and the seal” በተሰኘው መጽሐፉ ይህን ገልጦታል፡፡

“ታቦተ ጽዮን” ፤ “ኅዳር ጽዮን“ ፤ “አክሱም ጽዮን “ ክፍል -1

የታቦተ ጽዮን መንበር -አክሱም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓላት አንዱ “ኅዳር ጽዮን” ሲሆን የሚከበረውም ኅዳር 21 ቀን ነው፡፡ የበዓሉን አከባበር ፤ ጥንተ ታሪኩን፤ ንግስት ሳባ ፤ቀዳማዊ ምኒልክና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮችን በተከታታይ ክፍሎች እንመለከታለን፡፡ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን “ታቦተ ጽዮን” የፈጸመችውን ልዩ ልዩ ተአምራት ለምእመናን እያስተማረች በታላቅ ድምቀት የምታከብረው ቅዱሳት መጻሕፍትን መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ በደብረ ሲና አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከጾመና ከጸለየ በኋላ ዐሥርቱ ቃላተ የተጻፈበትን ጽላት /ታቦተ ጽዮን/ ከእግዚአብሔር እጅ ተቀበለ፡፡ “ታቦተ ጽዮን” የሚለውንም ስያሜ ያገኘችው ጽዮን ተብላ በምትጠራው የእስራኤል ከተማ ስም ነው፡፡ ጽዮን ማለት ተፀወነ፡- ተጠጋ፣ ተማጠነ ማለት ነው፡፡ ክቡረ ዳዊትም ጽዮንን አምባ፣ መጠጊያ አድርጎ ብዙ ጠላቶቹን ተዋግቶ አሸንፎ ድልን ተጎናጽፏል፡፡ አጼ ፋሲል በ16ኛው ክፍለዘመን ያሰሩት ቤተክርስቲያን ከፊት ለፊት እና በጎን ሲታይ ጽዮን የተባለችው የታላቁ የዳዊት ከተማ የተገፉና የተበደሉ ሕዝቦች ሁሉ እውነተኛ ፍርድ ለማግኘት፣ ተሰብስበው የሚሰነብቱባት ከተማ ስለነበረች፣ ጽላተ ሙሴም በዚያ ስለነበረች በርሷ ተማጽነውም ችግራቸው ሰለሚቃለል ታቦቷ “ታቦተ ጽዮን” ተብላለች፡፡ ዮሐንስ ፍቁረ እግዚእ በራእዩ “በሰማይ ያለችው የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተከፈተች፡፡ በውስጧም ያለችው ታቦተ ሕግ ታየች፡፡” ራእይ. 11 ሚ 19 በማለት የተናገረውን ቅዱስ ኤጲፋንዮስ በመጽሐፈ አክሲማሮስ ሲተረጉመው “በሥላሴ ጸዲል በሥላሴ ብርሃን የተመላች ስመ ሥላሴ የተጻፈባት ታቦት በኢየሩሳሌም ሰማያዊት አለች፡፡
በዚህች ታቦት ላይ ከፍጥረተ ዓለም በፊት ስመ እግዝእትነ ማርያም ተጽፎባት ነበር፡፡ ቅድመ ዓለም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከመፈጠሯ በፊት በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖረ ነበር የሚለው መሠረቱ ይህ ነው” ብሏል፡፡ ታቦተ ጽዮን የምትኖርበትን ድንኳን ሊቀ ነቢያት ሙሴ እንዲሠራ እግዚአብሔር ነግሮታል፡፡ ሊቁ ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ሲናገር “ደብተራ ኦሪትን በኢየሩሳሌም ሰማያዊት አርአያና ምሳሌ እንዲሠራ እግዚአብሔር አሳይቶታል፡፡ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት ሁለንተናዋ ከብርሃን የተሠራች ናት፡፡ የኢየሩሳሌም ሰማያዊት ቅርጽም ደብተራ ኦሪትን ትመስላለች፡፡” ይላል፡፡ ሕዝቡም ከፈጣሪያቸው ጋር ቃል ኪዳን ገብተው በታቦተ ጽዮን አማካኝነት ሲያመሰግኑ ኑረዋል፡፡ ታቦተ ጽዮን እግዚአብሔርን ለሚያምኑ፣ ሕጉን ትእዛዙን ለሚፈጽሙ ሰዎች ሁሉ ልዩ ልዩ ተአምራትን እንደፈጸመች ከቅዱስ መጽሐፈ እንረዳለን፡፡ እስራኤላውያን ሕጉን ሲጠብቁ ትእዛዙን ሲፈጽሙ እግዚአብሔር በታቦተ ጽዮን እያደረ ይረዳቸውና ጠላቶቻቸውንም ድል ያደርጉ ነበር፡፡ ሕጉን ሲያፈርሱ ደግሞ በጠላቶቻቸው ይሸነፉ ነበር፡፡ አጼ ኃይለሥላሴ ያሰሩት ቤተክርስቲያን - አክሱም በዚያ ዘመን ኤሊ የሚባል ሊቀ ካህናት ነበር፡፡ አፍኒንና ፊንሐስ የሚባሉ ሁለት ልጆች ነበሩት፡፡ እድሜውም 98 ዓመት ነበር፡፡ አፍኒንና ፊንሐስ የአባታቸውን ምክር አቃልለው የማይገባ ኃጢአት ሠርተው አምላካቸው እግዚአብሔርን አሳዘኑ በራሳቸው ፈቃድ ተጉዘው ሕገ እግዚአብሔርን ጣሱ፡፡ በሕዝቡም ላይ የሚያደርሱት በደል እየጨመረ ሔደ፡፡ አፍኒንና ፈንሐስ እግዚአብሔር በኃጢአታቸው ምክንያት በረድኤት ስለተለያቸው ፍልስጥኤማውያን በጠላትነት ተነሡባቸው፡፡ እስራኤላውያን ከኤሊ ልጆቸ ጋር ሆነው በአንድነት ታቦተ ጽዮንን ይዘው ለጦርነት ወደ ፍልስጥኤም ዘመቱ፡፡ ጦርነትም ገጠሙ ታላቅ ግድያም ሆነ፡፡ በጦርነቱ አፍኒንና ፊንሐስ ሞቱ፡፡ ታቦተ ጽዮንም በኤሎፍላውያን እጅ ተማረከች፡፡ ሕዝቡም በጦርነት አለቁ፡፡ ከጦርነቱ ያመለጠ አንድ ሰው ወደ ኤሊ ሄዶ እስራኤላውያን ተሸንፈው መሸሻቸውን፡ ሁለቱ ልጆቹ አፍኒንና ፊንሐስ መሞታቸውን ታቦተ ጽዮንም መማረኳን ነገረው፡፡ ኤሎፍላውያንም ታቦተ ጽዮንን ማርከው ከወሰዷት በኋላ ዳጎን ከተባለው ጣዖታቸው በታች አስቀመጧት፡፡ በማግስቱ የዳጎን አገልጋዮች መጥተው ቢያዩአት ፣ ዳጎን ከእግዚአብሔር ታቦት ፊት በግንባሩ ተደፍቶ አገኙት፡፡ አንስተው አቁመውት ሔዱና በማግስቱ መጥተው ቢያዩት በግንባሩ ወድቆ እጆቹ ተለያይተው ጣቶቹም ተቆራርጠው ደቀው በወለሉ ላይ ተበታትነው ነበር፡፡