Tuesday, January 31, 2012

በአንድ የዘመዴ ቤት አንድ ዘመዴ ቤት ሄጄ ነው፡፡ እናቱ «እስኪ ያንን ነገር ለዳንኤል አሳየው» አለቺው ልጇን፡፡ ልጇ የአራተኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡ ደብተሩን ይዞት መጣ፡፡ ትናንት ሠርቶ ዛሬ ባሳረመው የአማርኛ የቤት ሥራ ሁለት ኤክስ አግኝቷል፡፡ ልጁ ግን ለምን ኤክስ ሊሆን እንደቻለ ሊገባው አልቻለም፡፡ እናቱን ደጋግሞ ጠየቃት፡፡ እርሷም ግልጽ አልሆነላትም፡፡ የተሰጠው ጥያቄ አዛምድ ነው፡፡ እዚያ መካከል «እንደ ወትሮው» የሚል ሐረግ በ «ሀ» ሥር ይገኛል፡፡ በ «ለ» ሥር ደግሞ «እንደ ሁልጊዜው» የሚል ምርጫ አለ፡፡ ልጁ የመጀመርያውን ኤክስ ያገኘው እነዚህን በማዛመዱ ነበር፡፡ ከዚያው በታች በ«ሀ» ሥር ላለው «መሞከር» ለሚለው ቃል «መጣር» የሚል ተዛማጅ በ«ለ» ሥር ተቀምጧል፡፡ የሚል ሌላ አዛምድ አለ፡፡ ልጁ ከተሰጡት መልሶች ተቀራራቢ የሆነውን መልሷል፡፡ መምህሩ ግን አላረመለትም፡፡ እኔንም ጥያቄ ፈጠረብኝ፡፡ ይበልጥ ያስገረመኝ ደግሞ ትክክለኛው መልስ ምን እንደሆነ አለመጻፉ ነው፡፡ ልጁን «መልሱ ምንድን ነው አላችሁ?» ብዬ ጠየቅኩት፡፡ «ኤክስ አደረገኝ እንጂ መልሱን አልጻፈልኝም» አለኝ፡፡ መምህሩ ደብተራቸውን ወስዶ ኖሯል ያረመው፡፡ «እስኪ መጽሐፉን አምጣ» አልኩና ጥያቄዎቹን መመልከት ጀመርኩ፡፡ አሁን ነገሩ ግልጽ ሆነልኝ፡፡ ልጁ «መ»ን እና «ሠ»ን ሲገለብጥ አቀያይሯቸዋል፡፡ መምህሩም የአዛምዱን መልሶች ያረመው ፊደላቱን እያየ እንጂ መልሱን እያየ አይደለም፡፡ ይህ ግን በልጁ ላይ ሁለት ነገር ፈጠረበት፡፡ አንደኛ ለምን ኤክስ እንዳገኘ ሊገባው አልቻለም? ሁለተኛ ደግሞ የእነዚህን ሐረጋት ትርጉም ሊያውቅ አልቻለም፡፡ ምክንያቱም እርሱ ትርጉም ነው ብሎ የሰጠው መልስ ስሕተት ነው ተብሏል፡፡ ትክክለኛው ደግሞ አልተነገረውም፡፡
እኔ እዚህ ላይ ነበር ማሰብ የጀመርኩት፡፡ አሁን ይሄ ልጅ የሚጠበቅበት ምንድን ነው? የቃላቱን ትርጉም ማወቅ ነው? ወይስ በትክክል መገልበጥ? ለልጁ ሁለቱም ጥቅም አላቸው፡፡ የቃላቱን ትርጉም ማወቅ ዕውቀቱን፣ በትክክል መገልበጥ ደግሞ ክሂሎቱን ይጨምርለታል፡፡ ይህ የሚሆነው ግን መምህሩ ለልጁ ሁለቱንም ካስረዳው ብቻ ነው፡፡ የአዛምድ መልሶችን «እናሸንፋለን፣ ኢትዮጵያ ትቅደም፣ ሶሻሊዝም ይለምልም» እያለ ያመጣ የነበረው መምህሬ ትዝ አለኝ፡፡ ያንን ያደረገው አንድም ለማረም እንዲቀለው፣ አንድም ለዘመኑ ብሎ ይመስለኛል፡፡ እኔ መምህሩን ብሆን ኖሮ የመልስ ፊደል ብቻ እያየሁ አላርምም ነበር፡፡ ከመቶ በላይ ተማሪዎች በአንድ ክፍል በሚማሩበት ቦታ እና ዘመን ይህ ቢደረግ ለይቅርታ ልብ በኖረን ነበር፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው ግን ከሠላሳ በላይ ተማሪዎች በአንድ ክፍል ባልተቀመጡበት የግል ትምህርት ቤት ነው፡፡ መምህሩ የተማሪዎቹን ደብተር ወስዶ ማረሙ የሚመሰገን ነው፡፡ ግን ቤቱ ከወሰደው ላይቀር ተረጋግቶ ቢያር ምላቸው ምን ነበረበት? አንዳንዴኮ ልጆች ያልታሰበ መልስ ያመጣሉ፡፡ ከተለመደው ሁኔታም ሊያፈነግጡ ይችላሉÝÝ ይህንን ማየት የሚቻለው ልጆቹን በቅርበት በመከታተል እና ለእያንዳንዱ ተግባራቸው ትኩረት በመስጠት ነው፡፡ አያሌ የዓለም ሳይንቲስቶች ከትምህርት ቤት እየተባረሩ የወጡት መምህሮቻቸው ከተለመደው መንገድ ወጣ ብለው የተማሪዎቹን ችሎታ፣ ፍላጎት እና መንገድ ለማየት ባለመቻላቸው እና ባለ መፈለጋቸው ነበር፡፡ በተአምረ ኢየሱስ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስን የዕብራይስጥ ፊደል ሊያስተምረው የወሰደው መምህር የገጠ መውም ይሄው ነበር፡፡ «አሌፍ በል» አለው፡፡ «አሌፍ» አለ፡፡ «ቤት በል» አለው፡፡ ዝም አለ፡፡ መምህሩ ተናድዶ ይቆጣ ጀመረ፡፡ ያን ጊዜ ሕፃኑ ኢየሱስ ክርስቶስ «መጀመርያ የአሌፍን ትርጉም ንገረኝና ቤት እላለሁ» ብሎ መለሰለት፡፡ መምህሩ ግን ከተለመደው መንገድ መውጣቱ ስላስደነገጠው ለእናቱ ወስዶ ሰጣት፡፡ አንድ መምህር የነገሩኝን እዚህ ላይ ባነሳው መልካም ሳይሆን አይቀርም፡፡ እርሳቸው የአማርኛ መምህር ናቸው፡፡ የአማርኛ አባባሎችን አስተምረው ለተማሪዎቻቸው ጥያቄ ሰጧቸው፡፡ ከጥያቄው በአንዱ «የነ ቶሎ ቶሎ ቤት» የሚለውን አባባል ጀምረውን ተውት፤ ተማሪዎቹ እንዲያሟሉት፡፡ አንዲት ልጅ ታድያ የተለየ ነገር ይዛ መጣች፡፡ «የነ ቶሎ ቶሎ ቤት ሲሚንቶው አይደርቅም» ይላል መልሷ፡፡ «ገርሞኝ ለብዙ ደቂቃ አየሁት» አሉ መምህሩ፡፡ «እውነቷን እኮ ነው አልኩ፡፡ ትናንት ቤት በሣር በሚሠራበት ዘመን ግድግዳው ሰንበሌጥ የሚለው ትክክል ሊሆን ይችላል፡፡ ዛሬ ቤት በብሎኬት በሚሠራበት ዘመን ግን ይህ ሊሠራ አይችልም፡፡ በዚህ ዘመን ችኩል ቤት ሠሪ ሲሚንቶው ሳይደርቅ ቀለም ሊቀባ ነው የሚችለው ብዬ አሰብኩ፡፡ እናም ዝም ብዬ ተውኩትና ልጂቷን ጠየቅኳት፡፡ እኔ ያሰብኩትን ነበር የነገረችኝ፡፡ እንዲህ በማሰቧ ገርሞኝ አስጨብጭቤ አረምኩላት» ብለውኛል፡፡ መምህር እንዲህ ነው፡፡ መምህር እና ሰይጣንኮ ምንም ሁለቱም ቢፈትኑ ሁለቱ ግን አንድ አይደሉም፡፡ ሰይጣን ለመጣል ይፈትናል፣ መምህር ለማሳለፍ፤ ሰይጣን ያላስተማረውን ይፈትናል፣ መምህር ያስተማ ረውን፡፡ ሰይጣን መውጫውን ደፍኖ ይፈትናል፣ መምህር እያሳየ፤ ሰይጣን ተስፋ ለማስቆረጥ ይፈትናል፣ መምህር ተስፋ ለመስጠት፤ ሰይጣን ለማሳሳት ይፈትናል፣ መምህር ለማረም፤ ሰይጣን ለማደንቆር ይፈትናል፣ መምህር ለማሳወቅ፤ ሰይጣን ለማጣመም ይፈትናል፣ መምህር ለማቃናት፡፡ ልጁኮ ከመጽሐፉ ሲገለብጥ መሳቱን እኔ እስክነግረው ድረስ አልገባውም ነበር፡፡ ታድያ ምኑን ተማረው፡፡ ወይ መምህሩ ተሳስቷል ብሎ መምህሩን ይንቃል፤ ያለበለዚያም ደግሞ እራሱን ስሕተተኛ አድርጎ የተጣመመ ዕውቀት ይገበያል፡፡ ለቃላቱ እርሱ የሰጣቸው ፍቺዎች ስሕተት ናቸው ብሎ እንዲደመድም አድርጎታልና፡፡ ጥያቄ እና ፈተና ዋና ዓላማቸው መስተማር እና መመዘን ነው፡፡ ሰው ከስሕተቱ እንዲማር፡፡ የዕውቀት ደረጃውንም እንዲያውቅ፡፡ ያ የሚሆነው ግን ጥያቄዎቹ ግልጽ፣ ዕውቀትን ለመመዘን የሚያስችሉ እና በተማሪው ዐቅም የቀረቡ ከሆኑ ብቻ ነው፡፡ ትዝ ይለኛል ዐሥረኛ ክፍል እያለሁ የእንግሊዝኛ መምህራችን «say true or false´ የሚል ከሃምሳ የሚታረም ዐሥር የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርት ፈተና አመጣ፡፡ ደግሞ ጥያቄው እንዴት ቀላል መሰላችሁ፡፡ ሁላችንም ዐሥር ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ጨርሰን መለስን፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ በቀጣዩ ቀን ክፍሉ በድንጋጤ ነበር የተናጋው፡፡ ሁላችንም ዜሮ ማግኘታችን ተነገረን፡፡ የቁጣ እና የድንጋሬ ማዕበል ክፍሉን መታው፡፡ እንዴት? አልን ሁላችንም፡፡ መምህሩም አብራሩልን፡፡ «እኔ «say true or false» አልኩ እንጂ «write true or false» አላልኩም አሉን፡፡ «እና ምን ማድረግ ነበረብን?» አልናቸው፡፡ «ተናገሩ ነው የተባላችሁትና በቃላችሁ «true» «false» ማለት ነበረባችሁ ብለውን ዐረፉት፡፡ ፈተናው የተሰረዘው እስከ ዳይሬክተሩ ቢሮ በደረሰ ክርክር ነበር፡፡ ዋናው የትምህርት ዓላማው በተማሪዎቹ ዘንድ የጠባይ ለውጥ ማምጣት እንጂ የፈተና ቴክኒክ እና ታክቲክ እንዲያውቁ ማድረግ አይደለም፡፡ የኛ መምህር «write» እና «say» በሚሉ ቃላት መካከል ያለውን ልዩነት እንድንረዳው ፈልገው ከሆነ አንድ ወይንም ሁለት ጥያቄዎችን በዚያ መልኩ ማቅረብ ይበቃቸው ነበር፡፡ ተማሪ ስሕተቱን የማረሚያ ዕድል ሊያገኝ ይገባዋል፡፡ ስሕተት መጥፊያ ሳይሆን መማርያ እንዲሆን፡፡ የራሱን ስሕተት ማረም እንዲለምድ፡፡ ወድቆ መነሣት እንደሚቻል እንዲገነዘብ፡፡ መውደቅ መጥፊያ እየሆነ ብዙ ወዳጆቻችን በአንዲት ቀን ፈተና የሕይወታቸው መሥመር ወደማይፈልጉት ተቀይሮባቸዋል፡፡ ከአንዲት ቀን ፈተና መውደቅ ከሕይወት ጉዞ መውደቅ እየተደረገ በመወሰዱም አያሌ ዜጎቻችን ትምህርት አይሆነኝም እንዲሉ አድርገናቸዋል፡፡ ሰው ከወደቀ በኋላ ሌላ ተመሳሳይ ፈተና የማያዘጋጅ ሰይጣን ነው፡፡ ሰይጣን ሌላ የመውደቂያ ፈተና ነው የሚያዘጋጀው፡፡ ዓላማው ፈትኖ መጣል ነውና፡፡ መምህር ግን ከዚህ እጅግ በብዙ፣ እጅግ በሚሊዮን መለየት አለበት፡፡ ዓላማው ፈትኖ ማሳለፍ በመሆኑ፡፡ አንድ ተማሪ በአንድ ፈተና ሕይወቱ የሚፈተንበት ዘመን ሊያበቃ ይገባል፡፡ ዛሬ የተሳሳተውን ነገ የሚያርምበት ዕድል ማግኘት አለበት፡፡ እንዲያውም መምህሩ ከመፈተኑ በፊት ተማሪዎቹ እንዲጨብጡት የሚፈልገውን ዕውቀት ወይንም ክሂሎት መያዛቸውን በተለያዩ መመዘኛዎች እያገላበጠ ተማሪዎቹን መለካት አለበት፡፡ ፈተና ከዚያ በኋላ የሚመጣ ነው፡፡ በአንዳንድ ሀገሮች እንዲያውም የጥያቄ ባንክ የሚባል ነገር አለ፡፡ በአንድ የትምህርት ዓይነት እንዲጨበጡ የሚፈለጉ ነገሮችን አሟልተው የያዙ በተለያየ ዓይነት እና ቅርጽ የወጡ ጥያቄዎች ያሉበት ባንክ ነው፡፡ ተማሪዎቹ በዚያ ባንክ ያሉ ጥያቄዎችን በሙሉ ለመሥራት ከቻሉ ፈተናው አይከብዳቸውም፡፡ ምክንያቱም ራሳቸውን ፈትነው መጥተዋልና፡፡ የዚህ ምክንያቱ ፈተናን ለማቅለል አይደለም፡፡ ተማሪዎቹ በፈተናው ሰዓት ከዕውቀት እና ከክሂሎት ጋር እንጂ ከፈተና አወጣጥ ታክቲክ ጋር ሲሟገቱ እንዳይውሉ ለማድረግ እንጂ፡፡ አንዳንዴኮ ከጥያቄዎች እና ከፈተናዎች የምንማረው የሽወዳ ጥበቦችን እንጂ ክሂሎት እና ዕውቀትን አይደለም፡፡ አንዳንድ ጥያቄ አውጭዎችም እንዴት ተማሪዎችን ልሸውዳቸው እችላለሁ? ይላሉ እንጂ እንዴት ዕውቀታቸውን ልመዝነው እችላለሁ? አይሉም፡፡ እንዲያውም እንደ አስማተኛ ፊልም ሸዋጅ ፈተና የሚያወጡ መምህራን በአንዳንድ ቦታዎች እንደ ታላቅነት መለኪያ ተወስዶ ሲሞገሱበት ይሰማል፡፡ ሲከበ ሩበትም ይታያል፡፡ በትምህርት መቀለድ ለተማሪዎች የአራዳነት መለኪያ እንዳልሆነ ሁሉ ተማሪ መጣልም ለመምህራን የታላቅነት ማሳያ አይደለም፡፡ ቦንብ ማፈንዳት የሚጎዳውን ያህል ቦንብ ቦንብ ጥያቄዎችን ማውጣትም የተማሪን ሕይወት ይጎዳል፡፡ እዚያ ቤት ቁጭ ብዬ ነበር ይህንን ሁሉ የማስበው፡፡ ሌሴቶ ያኘሁት አንድ ወዳጄ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያስተምር በነበረበት ጊዜ ለተማሪዎቹ የሚያደርገውን እና ሌሴቶ ዩኒቨርሲቲ የሚያደርገውን እያነፃፀረ «ግፍ ሳንሠራ አልቀረንም» ይል ነበር፡፡ እዚያ ከአንድ ፈተና በፊት ሦስት ተመሳይ ፈተናዎችን አውጥቶ የተማሪዎችን ብቃት መለካት ነበረበት፡፡ ከዚያም አብዛኞቹ የተሳሳቱባቸውን መርጦ እንደገና ማስተማር፣ በተለየ መንገድም ትምህርቱን ማቅረብ ነበረበት፡፡ ወደ ፈተና የሚገባው ቢያንስ ሰማንያ አምስት በመቶው ተማሪዎች ያወጣቸውን ሁሉንም ጥያቄዎች ሲመልሷቸው ነው፡፡ «እንዲህ ብናደርግ ኖሮ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ስንቱን ለክብር እናበቃው ነበር» እያለ ይቆጫል ሁልጊዜ፡፡ እዚያ በዘመዴ ልጅ ላይ እንደተደረገው በተማሪዎቹ የጥያቄ ደብተር ላይ ኤክስ ማድረግ ብቻ አይበቃም፡፡ ለምን ኤክስ እንደሆነ ማብራራት እና ተማሪው ያንኑ ዓይነት ጥያቄ በሌላ መንገድ ተጠይቆ ስሕተቱን እንዲያስተካክል ማድረግም ይፈለጋል፡፡ ያኔ ነው ታድያ መምህሩ በስተ መጨረሻ «ለወይኔ ያላደረግኩለት ነገር ግን ላደርግለት የሚገባ ምን ነገር አለ?» ብሎ መናገር የሚችለው፡፡

No comments:

Post a Comment